ልጅ ቴዎድሮስ ፍቅረማርያምን ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቅኩት ከጥቂት ወራት በፊት ሰናይት በተባለች የጋራ ፌስቡክ ጓደኛችን በኩል ነበር። አንድ የዓፄ ቴዎድሮስ ፎቶ ፌስቡክ ላይ ለጥፌ ወዳጄ መሸሻ ካሣን ታግ አደረግኩት። ሰናይት ደግሞ እዛው ፎቶ ላይ ልጅ ቴዎድሮስን ታግ አደረገችው። እሱም ከዓፄው ጋር ዝምድና እንዳለው ነግሮኝ እንዲያብራራልኝ ብጠይቀው የዘር ሐረጉ ከቓራው ካሣ ቀጥታ ተመዞ ተገኘ።

ልጅ ቴዎድሮስ ፍቅረማርያም በዘር ሀረጉ ይኮራል እንጂ አይመፃደቅም። የንጉሥ ዘር ነህ ብለው ኧረ ተራ ሰው ነኝ እያለ ይመልስልኛል። እንዲውሁ በጨዋታ መልክ እያልን ስለ ቴዎድሮሥ ብዙ ለማወቅ ችያለሁ። ብዙ ውጣ ውረድ ፣ ድካም  አሳልፏል። በሰባት ዓመቱ ከሀገሩ ተሰድዶ ባህሉን በአግባቡ ሳያጣጥም አድጓል። እንዲያው ብዙ ነገሩ አሜሪካዊ እንጂ ሃበሻ አይመስልም። ቓንቓም ቢሆን ትንሽ ይከብደዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ልቡ ከሀገሩ አልተለየም። ስለ ኢትዮጵያውያን ስቃይ ፣ ስለ ፍትህ ልቡ ይጨነቃል። እሱ ያሳለፈውን ከባድ ጊዜ ስለማይረሣ የድሃው ብሶት ይሰማዋል።

አሜሪካን ሃገር እያደገ በነበረበት ወቅት ባህሉን መልመድ ያዳግተው ነበር። ቢሆንም ያንን አልፎ በአሜሪካ ከሚገኙ ታላላቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቓማት ከሆኑት ከጆርጅ ሜሦን እና ከጆን ሆፕኪንስ የመጀመርያ እና የሁለተኛ ዲግራ ማዕረጉን አጠናቓል። ከዚያም በአንድ አንጋፋ መሥሪያ ቤት ውስጥ በአማካሪነት ሞያ ተቀጥሮ ሲሰራ ከቆየ በዃላ የዛሬ አራት ዓመት በደረሠበት ድንገተኛ ችግር ፣ ከቤቱ ተፈናቅሎ ጎዳና ላይ ወደቀ። ከጊዜያት በኋላ አንድ ዌሊንግተን ኮሎራዶ ውስጥ ወደሚገኝ መጠለያ ሚሢዮን ለመሸጋገር በቃ። እዛ በነበረው ቆይታ ከፈጣሪው ጋር እንደተቀራረበ ይነግረኛል። የአባቱ ሞት ፣ ያሳለፈው ውጣ ውረድ ደጋግሞ ይታወሰው ነበር። እኔ እሄን ስሰማ ትዝ ያለኝ አፄውም ገዳም ገብተው ሕይወትን ሲያሰላሥሉ ከፈጣሪያቸው ፣ ከመለኮታዊ ተልዕኮአቸው መቀራረባቸው ነበር። ልጅ ቴዲም እንደዛው። እንደውም ባናገርኩት ቁጥር የዓፄው ሕይወት በእርሱ ላይ ተንፀባርቆ ብልጭ ይልብኝ ጀመር። ሁለቱም የነገሥታት ዘር ይዘው ተወልደው ከምንም ያልተቆጠሩ ፣ ሁለቱም ኩሩ ኢትዮጵያን ፣ ሁለቱም በእግዜአብሔር ቸርነት ከመከራ ጊዜ ወጥተው ተልዕኮኣቸውን ለመፈፀም የተሰለፉ።

ንጉሰ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ በንግሥተ ሳባ እና በሰለሞናዊው ሥርወ መንግሥት ሥም ታንፀው የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያቆዩ ፣ ነገሥታት በሆድ አደርነት በቆዘሙበት ዘመን ፣ እሳቸውልቀው ወጥተው ፣ ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ ጀግና ነበሩ። ራስ ካሣ ሀይሉ የተወለደባት የዘመነ መሣፍንቷ ኢትዮጵያ ጥቂት መኳንንቶች በሕዝቡ ላብ እና ድካም የከበሩባት ፣ መሣፍንት በጥጋብ ያበዱባት ኢትዮጵያ ነበረች።

ካሣ ሀይሉ ግን የከበረው ለሕዝብ በመቆም ፣ ድሀውን በመደገፍ ነበር። ቴዎድሮስ ተብሎ ከነገሠ በኋላም በፍትህ ታንፆ ፣ በሕዝቡ ተወዶ ፣ ሀገሩንም ወዶ ፣ በመቅደላ ጦርነት በኢንግሊዝ ወራሪዎች ላለመበገር እራሱን ሰውቶ ፣ ሀገሩን ያቆመ ጀግና ነበር።

ታድያ የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስንመለከት የዘውድ ስርዐቱ በ1966 መፍረሱ ከሃገራችን አልፎ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ  ያደረሰው ጦስ ለብዙዎቻችን ግልፅ ነው። የሀገራችን ታላቅ ልዒቃን በአንድ ክፉ ሌሊት የተረሸኑበት ፣ ኢትዮጵያን ከፋሽስት እጅ ለማስጣል የተጋደሉት ጃንሆይ የተከዱበት ፣ 500,000 ኢትዮጵያውያን በግፍ የረገፉበት የደርግ ክፍለ ዘመን ለብዙዎች አሁንም የቅርብ ትውስታ ነው። ላለፉት 44 ዓመታት ሕዝባችን የሚያውቀው ቁስል እና ስቃይ ነው።

እንደውም ልጅ ቴዎድሮስ ጃንሆይ በወረዱ በወራቸው መወለዱን ሳስበው እንደርሱ እድሜያቸውን ሙሉ ኢትዮጵያን በቀውስ ገፅታዋ ብቻ የሚያውቋት እንዳሉ አልዘነጋም። እናማ ልጅ ቴዎድሮስ በፋሲካ መልዕክቱ እንደተናገረው አሁን ኢትዮጵያ የምትፈልገው ገንዘብ ፣ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ መድሃኒት ነው። የተረጨው የዘር ጥላቻ መርዝ እርስ በርስ ሊያጫርሰን ይኸው አንድ ማግስት ይቀረዋል። ‘ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሣሩ’ እንዲሉ መሪዎቻችን ዳግም ዘመነ መሣፍንት ለኩሰውብናል። የደርግ ቡርዥዋ ጠል ፖለቲካ ሳይቀር የኢህአዴግ ዐምሐራ ጠል ፖለቲካ ፣ አሁንማ ፖለቲካውን የሚያራምደው መንግሥት ሳይሆን ግለሰብ ሆኗል።

እንደኔ እንደኔ ግን አሁን ከዘር አጥር አሻግሮ አንድ የሚያደርገን ፣ ታታሪነትን የሚያስተምረን ፣ አዲስ ቴዎድሮስ ያስፈልገናል። በበኩሌ ድጋፌን ለልጅ ቴዎድሮስ እሰጣለሁ ፣ ፖለቲካን ሳይሆን ፍቅርን እንዲያስተምረን።

በነገራችን ላይ ፈጣሪ ለዓፄ ቴዎድሮስ ተዋበች የምትባል ንግሥት እንዳደለው ለልጅ ቴዎድሮስም ቤተለሔም በቀለ የተባለች ድንቅ ባለቤት ሰጥቶታል።
የወደፊቱንማ ከእግዜር ውጭ ማን ያውቃል።

በግሌ ግን ልጅ ቴዎድሮስ ከሚመራው ኢትዮጵያውያን ለሕገመንግሥታዊ ንጉሣዊ ሥርዐት (ኢሕንሥ) ከተባለው ድርጅት ጎን ቆሜ፣ የኢትዮጵያን ነገሥታት በሕግ አጥር ገድቦ ዳግም የሚወልደውን እንቅሥቃሴ ለመለኮስ በታላቅ ክብር አገለግላለሁ።

እኔ በግሌ የኢትዮጵያን ዘውድ ክብር ለማስመለስ ከሌሎች ጋር ስሰራ ብዙ ዘመን ሆኖኛል። ከኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤትም ጎን ቆሜ ልዑል ኤርሚያስ ሳሕለ ሥለሴ ላለፉት 33 ዓመታት የዘውዱን ክብር እና በጎ ስም ለመጠበቅ ሲረባረብ ከኋላው ሆኜ በተቻለኝ ዐቅም ለመደገፍ ሞክሪያለሁ። አሁን ደግሞ ከመቼውም በላይ ሁላችንም የግል ጥቅማችንን ትተን ፣ በአንድ ኢትዮጵያ ፍቅር ታንፀን ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይበጃል ያልነውን የምናበረክትበት ጊዜ ደርሧል። እንደኔ እምነት የኢትዮጵያን ዘውድ የሚወድ ፣ ዘውዱን ወደ ክብሩ ለመመለስ የሚሠራ ሁሉ ፣ የኢትዮጵያውያን ወዳጅ ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ የንጉሥ ሥርዐት ተዘርግቶ ለማየት የሚሻ ሁሉ አንድ ላይ ቢሰራ ኢትዮጵያ አፍሪካዊትዋ ጃፓን የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለም። የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር በሞራል እና በፍቅር የታነፀ ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፣ ብቁ አመራር ብቻ ነው። ታድያ ከገባንበት የዳግም ዘመነ መሣፍንት ጦስ አውጥቶ ፣ እርስ በርስ ስንባላ ‘ተው’ የሚለን መሪ ከመይሣው ዘር ሌላ ወዴት እንፈልግ?
ለዚህ ነው አሁንም ከልጅ ቴዎድሮስ ጎን ቆሜ ለመታገል ዝግጁ ነኝ የምለው። ምንም እንኳን ቓንቓ ቢከብደውም ፣ ምንም እንኳን እንደኛ ህዝብ የተሰማውን የሚደብቅ ባይሆንም ልጁ እድል ይሰጠው ባይ ነኝ። ደሞሳ ‘መንገድ ሲዘጋ አካሄዱን የማይቀይር እብድ ብቻ ነው’ አይደል የሚሉት ፈረንጆች? ለማንኛውም የልጅ ቴዎድሮስ እና የባለቤቱ በሆነው ‘ግዮን ጆርናል’ በተባለው ድረ ገፅ የተለጠፈውን የቪዲዮ መልዕክት እዚህ በመጫን ማግኘት ይችላሉ።

በማጠቃለያም ፣ እንደምናውቀው ኢትዮጵያን ካተራመሱ የታሪክ ትዕይንታት መሃከል አፄ ዮሃንስ ዓፄ ቴዎድሮስን ከድተው ለኢንግሊዝ ጦር የማጋለጣቸው ጉዳይ ይጠቀሳል። ታድያ ልጅ ቴዎድሮስ እና ባለቤቱ ቤተልሔም በቀለ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወንድ ልጅ ወልደው ፣ በእግዜአብሔር ፍቃድ ‘ዮሃንስ ቴዎድሮስ’ ብለው ይጠሩታል። ልጁንም ወላጆቹንም ይባርክልን። እናማ አዲስ ትውልድ ስንረከብ አሮጌ ቁሥሎች እንዲድኑልን እየተመፀንኩኝ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ባርኮ በክብሯ  ያቆያት በማለት እዘጋለሁ።

Read this article in English by clicking HERE and listen to a personal message from Lij Teodrose Fikremariam to all Ethiopians and supporters of Ethiopia around the world.